ስሜታችን ላይ ተጽእኖ የሚያመጡ ነገሮች
(“ገዢው ስሜት” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ)

በስሜታችን ላይ ተጽእኖ ስላላቸው ነገሮች ስናስብ ምናልባት ሁኔታውን ከትናንትና፣ ከዛሬና ከነገ አንጻር ብናጤነው የጠራና ግልጽ እይታ ይኖረናል፡፡ ስሜታችን ከእውነታ ወይም ከእውነታ-መሰል ነገሮች ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ እውነታዎች ወይም እውነታ-መሰል ሁኔታዎች ደግሞ ካሳለፍነው፣ በማለፍ ላይ ካለነው ወይንም ደግሞ ወደፊት ይሆናል ብለን ከምናስበው ነገር ጋር ይነካካሉ፡፡

የስሜትን መንስኤዎች በዚህ መልኩ በትኖ መመልከቱ ስሜታችንን በሚገባ እንድንገነዘበው ይረዳናል፡፡ ይህ የስሜትን መንስኤ ከትናንቱ፣ ከዛሬውና ከነገው አንጻር ለማወቅ የምንጠቀምበት ሂደት ቀለል ያለው አቀራረብ ሲሆን፣ ምናልባት ሁኔታውን ከህክምናውና ሌሎች ጠለቅ ካሉ መንስኤዎች አንጻር ማየት የሚያስፈልግበትም ጊዜ እንዳለ አስታውሶ ማለፉ ተገቢ ነው፡፡

1.  የትናንቱ - የስሜት መልህቆችና ትዝታዎች

በስነ-ልቦናው አለም “መልህቆች” (Anchors) በመባል የሚታወቁ በስሜታችን ላይ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች፣ እንደ ስእል፣ ድምጽ፣ ሽታና ጣእም የመሳሰሉ ከአንድ ስሜት ጋር ተቆራኝተው በውስጣችን ልክ እንደ መልህቅ ቸክለው የተቀመጡ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ አንድን ጣእም ስንቀምስ፣ ከዚያ ጣእም ጋር ተያይዞ በውስጣችን እንደተቀመጠው የስሜት “መልህቅ” አንጻር አንድ ደስ የሚል ወይም ደስ የማይል ስሜት ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህም ይህ ጣእም እንደ መልህቅ በውስጣችን በመተከልና በመቀመጥ በማንኛውም ሰዓት ያንን ስሜት ሊያመጣብን ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ ሽታዎች፣ ድምጾችና አካባቢዎች እንደመልህቅ ሆነው የመተከልና ከአንድ ስሜት ጋር የመያያዝ ባህሪይ አላቸው፡፡

“መልህቆች” በውስጣችን የሚቀመጡና ባየናቸው፣ ባሸተትናቸው ወይም በቀመስናቸው ቁጥር አንድን ጠንካራ ስሜት የሚያመጡን ልምምዶች ናቸው፡፡ ስለሆነም፣ አንድን የማንፈልገውን ጤና ቢስ ስሜት ለመገንዘብ፣ ምንጩን ለማወቅና ቀስ በቀስ መፍትሄን ለመፈለግ በምናደርገው ጉዞ መልህቁን ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ መንስኤውን ያላወቅንለትን ችግር ስሩን ማግኘት ስለማንችል መፍትሄው ላይላዩንና ጊዜያዊ ይሆንብናል፡፡

2.  የዛሬው - ልምምዶችና ልማዶች

አሁን ያለህበትን የወቅቱን ሁኔታህን ስትመለከተው ምናልባት በወቅቱ የሚሰሙህን አዎንታዊም ሆኑ አሉታዊ ስሜቶች መንስኤ የሚጠቁሙህን ልምምዶች እንዲሁም ልማዶች ታገኛለህ ብዬ እጠረጥራለሁ፡፡ ለምሳሌ፣ ማየትን የምታዘውትራቸውን ፊልሞች ማሰብ ትችላለህ፡፡ ምናልባትም ከፍርሃት ጋር የተያያዙ ፊልሞችን መመልከት ታዘውትራለህ እንበል፡፡ እነዚህ ፊልሞች ለስሜትህ ልክ እንደምግብ ናቸው፡፡ በሌላ አባባል፣ ፍርሃትን የሚያነሳሳ ነገር በአይን ይገባል፣ ፍርሃት ይመረታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በወቅቱ የምታገኛቸውን ሰዎች፣ አብዛኛውን ጊዜ የምታሳልፍባቸውን ቦታዎችና የተለያዩ እነዚህን መሰል ሁኔታዎች በሚገባ ብታጤናቸው ከስሜትህ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ትደርስበታለህ፡፡

ስለሆነም፣ በየቀኑ የምትሰማቸው፣ የምታያቸውና የምትለማመዳቸው፣ እንዲሁም ደግሞ የለመድካቸው ነገሮች በስሜትህ ላይ ታላቅ ተጽእኖ አላቸው፡፡ እዚህ ጋር ሳይጠቀስ ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ የጤንነትህ ሁኔታ ነው፡፡ የአንዳንድ ሰዎች የስሜት መቃወስ መንስኤው ከስነ-ልቦና ወይም ከአእምሮ ጤንነት ጋር የተያያዘ ሁኔታ ሊሆን ስለሚችል የባለሞያን ጣልቃ ገብነት የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

3.  የነገው - እቅዶችና እይታዎች

ዛሬ ሶስት ነገሮችን ተሸክሟል፡- በሃሳባችንና በትዝታ ማእከላችን ዛሬ የምንኖረው የትናንትናው ሁኔታ አንዱ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ የዛሬውና የወቅቱ ልምምዳችንና ልማዳችን ከዚያ ጋር ይደመራል፡፡ በመጨረሻም ገና ያልመጣውን ነገን ጎትተን በዛሬው የሕይወታችን ክፍል ውስጥ ስፍራ የመስጠታችን ሁኔታ ይታከልበታል፡፡ እነዚህ ሶስት ሁኔታዎች፣ “ዛሬ” ብለን በምንጠራው ዳግም ላይመለስ አንድ እድል ሰጥቶን በመጣ የጊዜ ገደብ ውስጥ ይተራመሳሉ፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች በቅጡ ማስተናገድ በስሜታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡  

ስለነገ ስታስብ ምን ይሰማሃል? ገና ስላልመጣው ነገር በማሰብ ትጨናነቃለህ? ለነገው ተገቢን እቅድ በማውጣትና ያንን በመከተል ተረጋግተሃል ወይስ ፊትህ ቀድሞ የመጣውን በማድረግ የተዘባረቀ የወደፊት ይታይሃል? ይሆኑብኛል ብለህ የምትሰጋባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ይሆኑልኛል ብለህ የምትናፍቃቸው ተስፋዎችህስ ምንድን ናቸው? እነዚህና እነዚህን መሰል ከነገ ጋር የተገናኙ ሃሳቦች በዛሬው ስሜትህ ላይ ጤናማ ወይም ጤና-ቢስ ተጽእኖ እንዳላቸው አትዘንጋ፡፡  
 

Comments

Popular posts from this blog

የግዕዝ ምሳሌያዊ አነጋገሮች