ውልደቱ ጎጃም ሲሆን ለቤተሰቡ አራተኛ ልጅ ነው ። ከውልደቱ ጎጃም ይልቅ ሐመሮች ማርከውታል። በሐመሮች መማረክ ብቻ ሳይሆን በብዕሩ ተከታታይ መጻሕፍት ደርሶላቸዋል። አስጊጦ ጽፎላቸዋል ። ፍቅረማርቆስ ደስታ በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን በብሔረሰቦች ባህል ላይ ያተኮሩ ተከታታይ መፃህፍትን ያበረከተ ደራሲ ነው። 'ከቡስካ በስተጀርባ'፣ 'ኢቫንጋዲ'፣ 'የዘርሲዎች ፍቅር'፣ 'አቻሜ' ና 'የንሥር ዓይን' የተሰኙት በሐመር ብሔረሰብ ታሪክ ላይ ያተኮሩት መጻሕፍት የብሔረሰቡን ባህል ና ትውፊት ከማስተዋወቁም በላይ የህዝቡን ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በድርሰቶቹ ያሳየን ደራሲ ነው ። ፍቅረማርቆስ የሐመር ብሔረሰብን ባህል የማስተዋወቅ ሥራውን አጠናክሮ በመቀጠል ለውጪው ዓለም አንባቢያን የሚሆን ሥራውን በእንግሊዝኛም አሳትሟል ። ይዀው ''Land of the Yellow Bull'' የተሰኘው መጽሐፉ በመላው ዓለም ተሰራጭቷል። 'የበጋው መብረቅ' በጃግማ ኬሎ የህይወት ታሪክ ላይ ያጠነጠነ መጽሐፍም ጽፏል ።
በሀገራችን በመጽሐፍ ታሪክ ውስጥ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ ታትሞ ለሕዝብ ከቀረቡ መጻሕፍት መካከል የእሱ መጻሕፍት ተጠቃሽ ናቸው ። ከ''መቶ ሺህ'' በላይ መጻሕፍቱ ታትመው ለገበያ ቀርበው ተሽጦለታል ። አምስት መጻህፍቶቹ በገበያ ላይ ሲውሉ ከአንድ በላይ የመታተም ዕድልን አግኝተዋል ። የመጀመሪያ መጽሐፋ [ከቡስካ በስተጀርባ] ሰባት ጊዜ ታትሟል ፤ ሁለተኛው [ኢቫንጋዲ ] አምስት ጊዜ ፣ ሦስተኛው [የዘርሲዎች ፍቅር] አራት ጊዜ ፤ አራተኛው [አቻሜ ] ሁለት ጊዜ ፤ አምስተኛውም[ የንሥር ዓይን] እንዲሁ ሁለተኛ ጊዜ ታትሟል ። ስድስተኛው መጽሐፉን ለየት የሚያደርገው በእንግሊዝኛ መታተሙ ነው ። የሃምሳ ሁለት ዓመቱ ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ የራሱን ስራዎች ሰብስቦ በእንግሊዝኛ ሲያሳትም በረዥም ልቦለድ ታሪክ ሶስተኛው ሰው ነው ።
Comments
Post a Comment