ውስጥህን ትንንሽ ሀሳቦችን በማሰብ አታጨናንቀው።
ትንንሽ ሀሳቦች የትም አይወስዱህም። የትም አያደርሱህም። ምንም አይለውጡህም። ትልልቅ ሀሳቦች ግን ትልልቅ ቦታ ያውሉሀል። ትልቅ እንድትሆንም መንገድህን ይጠርጉልሀል። ከውስጥህ የምታመነጫቸው ትልልቅ ሀሳቦች ከራስህ አልፎ ዓለምህን ይቀይራል። ትልልቅ ሀሳቦችን ማሰብ ስትጀምር ትልቅ ትሆናለህ።
ትንንሽ ሀሳቦችን በውስጥህ አጭቀህ ትልቅ ልትሆን አትችልምና ከውስጥህ ያሉትን ልቅምቃሚ ትናንሽ የማይረቡ ሀሳቦች አራግፈህ ጣላቸው። ያኔ ከውስጥህ ትልልቅ ሀሳቦች መብቀል ይጀምራሉ። በውስጥህ የሞላው ትናንሽ ሀሳብ ለትላልቆቹ ሀሳቦች ቦታ እንዲለቅ አድርገው።
ይህንን ሀሳብ የሚያጠነክርልኝ ምርጥ የፍራንክሊን ዴ ላኖ ሩዝ�ቬልት አባባል እንካችሁ፤
‹‹ታላላቅ ጭንቅላቶች በታላላቅ ሃሳቦች ላይ ይወያያሉ፣ መካከለኛ ጭንቅላቶች በክስተቶች ላይ ይወያያሉ፣ ትንንሽ ጭንቅላቶች ስለግለሰቦች ህይወት ያወራሉ፡፡›› አባባሉ እውነት አለው። ምንም እንኳን ፍራንክሊን ሩዝቬልት በህይወታቸው ብዙ ችግሮች ቢኖርባቸውም በውስጣቸው ያስቡ የነበረው ትልቅ መሆንና ትልቅ ነገርን መስራት ነበርና እንደሀሳባቸውም የታላቋ አሜሪካ የቁርጥ ቀን መሪ ሆነዋል። አንተስ፣አንቺስ ዛሬ ምን እያሰባችሁ ነው? አዎ ሀሳባችሁ የነገውን እናንተነታችሁን ለመወሰን ትልቅ ሀይል አለው። ስለዚህ በሀሳቦቻችን ላይ ጥንቃቄ እናድርግ። ትንንሽ ሀሳቦችንም ትተን ትልልቅ ሀሳቦችን ውስጣችንን እንሙላው! ያኔ ስለ ሌሎች ማብሰልሰላችንን ትተን በራሳችን ትልቅ ስኬት እንጠመዳለን። ይህም የማይታመን ትልቅ ለውጥን ያጎናጽፈናል።
Comments
Post a Comment