✨ሁላችንም በዓለም ላይ ቦታ አለን!
(We all have a place in the world)
☀️ወዳጆች በዚች ዓለም ላይ ሁላችንም ቦታ አለን፡፡ ዋናው ነገር ቦታውን የመለየት ብልህነቱና አስተዋይነቱ ነው፡፡ የሠው ልጅ በዚች ዓለም ላይ ሲኖር በዓለም ላይ ስሙን በክፉ አልያም በደግ ተክሎ የማለፍ ብቃት አለው፡፡ በታሪክ በክፋታቸው የተመዘገቡ ሠዎችም ቢሆኑ ለመጪው ትውልድ የሚሠጡት ትምህርት፣ ለሌሎች የሚያስቀስሙት ቁምነገር አላቸው፡፡ የጎልያድ ማአለብኝነት በትንሽ ጠጠር እንደሚተነፍስ ታሪኩ ቁምነገር ያስጨብጠናል፡፡ ትልቅ የሚመስል ትንሽ፤ ትንሽ የሚመስልም ትልቅ የሚሆንበት ዓለም ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ጎልያድም ሆነ ዳዊት እንደየባህሪያቸውና ስራቸው የሚሠጡን ትምህርት አላቸው፡፡ ቦታቸው የተለያየ ቢሆንም እኛ ከቦታቸው ትምህርት እንቀስማለን፡፡
🔑የእዮብ ትዕግስት ፈታኝ ቢሆንም እንኳን በመጨረሻ የተጎናፀፈው ደስታ ግን ለሁላችንም አስተማሪ ነው፡፡ ትዕግስት መጨረሻዋ የደስታ ፍሬ እንደሆነ ያሳያልና፡፡ የፈርኦን ትዕቢትም ምን ያህል ዋጋ በሕይወቱ እንዳስከፈለው የሚያስጨብጠን ዕውቀት አለው፡፡ ትዕቢተኞችን ትዕቢታቸው እንደሚጥላቸው ሲያስተምረን፤ ቅኖችን ደግም ቅንነታቸው ከፍ እንደምታደርጋቸው እንደየስራ ቦታቸውና እንደታሪክ አቀማመጣቸው እንማራለን፡፡
☀️ጃን ፖል ሳርተር የተባለው የህላዌነት (Existentialism) ፍልስፍና አራማጅ ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
🌘‹‹በሕይወት መገኘት የሚሠጠው ተፈጥሮ ነው፡፡ ለምሣሌ ተራራ ለምንነቱ ተፈጥሮ ከሠጠው ትርጉም ውጪ ምንም አዲስ ነገር ሊፈጥር አይችልም፡፡ ተራራ ሁሌም ተራራ ብቻ ነው፡፡ ሠው ግን ተፈጥሮ ሠውነትን ብቻ ሲሠጠው እሱ ግን በተጨማሪም ለራሱ ምንነት ትርጉም ይሠጣል፡፡ ወታደር ወይ ቄስ፤ ወይ አስተማሪ ይሆናል፡፡ ተፈጥሮ አንዴ ይፈጥረዋል፡፡ እሱ ደግሞ ራሱን በራሱ ይፈጥራል፡፡››
🔆እውነት ነው! አምላክ ሠውን ፈጠረ፡፡ ሠው ደግሞ አስተሳሰቡን መልሶ ፈጠረ፡፡ በአስተሳሰቡም የእጁን ፍሬ በደግም ይሁን በክፉ ለራሱም ይበላል፤ ለሌላውም ያጎርሳል፡፡ ሠው ከሌሎች ተፈጥሯዊ ነገሮች የሚለየው ትልቁ ጉዳይም በሃሳቡ ራሱን መልሶ መላልሶ መስራት መቻሉ ነው፡፡ የሠው ልጅ በዚህ ድንቅ ተፈጥሮው ዓለም ላይ ጥሎ የሚያልፈው ሠናይም ሆነ እኩይ ስራ አለው፡፡ ይሄ ስራው በራሱ ላይ የሚፈጥረው ውጤት እንዳለ ሆኖ ዓለም ላይም ቦታ ይዞ ለመጪው ትውልድ ትምህርት ይሠጣል፡፡ ክፉን በክፉነቱ፣ መልካምን በመልካምነቱ ተምሮ ከክፉው የሚሸሽና መልካሙን አጥብቆ የሚይዝ ተማሪ ግን እሱ ብልሁ ተማሪ ነው፡፡
✨ሁላችንም በዚች ዓለም ላይ ቦታ አለን፡፡ ቦታችንን የምንወስነው ግን እኛው ራሳችን ነን፡፡ ቦታውን አሠላስሎ፣ ክፉን ደጉን ለይቶ የመወሠን ሰልጣኑንና የማገናዘብ አቅሙን ተፈጥሮ ቸሮናል፡፡ እርግጥ ነው የሠው ልጅ በአስራአንደኛው ሠዓትም ቢሆን የነበረበትን ቦታ የመለወጥም ታላቅ ችሎታ አለው፡፡ አንዳንዱ ከነበረበት ከፍታ ራሱን ዘቅዝቆ ይጥላል፡፡ ብልሁ ደግሞ ከቁልቁል ቦታው ተነስቶ ከፍታው ላይ ጉብ ይላል፡፡ ሠው ይሄን ችሎታውን ለበጎ የመጠቀም ፋንታውም፣ ምርጫውም፣ ውሳኔውም እጁ ላይ ነው ያለው፡፡ በዚህ ምርጫውም የራሱን ቦታ ይይዛል፡፡
ጆርጅ በርናንድ ሾው ይሄን ሃሳብ ሲያጠናክር እንዲህ ይለናል፡-
⚜️‹‹ቀና አመለካከት ያላቸውም፣ ጨለምተኛ አመለካከት ያላቸውም፤ ሁለቱም ሠዎች ለሕብረተሰባችን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ቀና አመለካከት ያላቸው አይሮፕላን ሲፈጥሩ፤ ጨለምተኞቹ ደግሞ ፓራሹት ፈልስፈዋል፡፡››
በማለት ሁለቱም ጥጎች የራሳቸው ትሩፋት እንዳላቸው ይገልጻል፡፡
🔑ወዳጆች በአጠቃላይ ቦታ የሌለው ማንም የለምና ቦታችንን ለበጎ ዓላማና ለመልካም ስራ እንለይ የዛሬው መልዕክት ነው፡፡
✨የት ነው ቦታችን?? ከቅኖች ረድፍ ወይስ ከጨለምተኞች ጥግ?? መልሱን ለራሳችን!
ቸር ጊዜ!
✍️እብይ
✨💫🔑✨💫🔑✨💫🔑✨💫🔑
የግዕዝ ምሳሌያዊ አነጋገሮች
የግዕዝ ምሳሌያዊ አነጋገሮች.....#share *ኢይከብር ነቢይ በሀገሩ ነቢይ በሀገሩ አይከበርም። *መዐር አይጥዕሞ ለአድግ ለአህያ ማር አይጥማትም *አድኅን ርእስከ ራስህን አድን *አፍ ይጼውአ ለሞት አፍ ሞትን ይጠራል *ለሰሚዕ እጽብ ለሰሚው አስደናቂ *ብላዕ በሐፈ ገጽከ ጥረህ ግረህ ብላ *አክብር አባከ ወእመከ አባትና እናትህን አክብር *ተፋቀሩ በበይናቲከሙ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ *ኀላፊ ንብረት፣ክመ ጽላሎት ሀብት እንደ ጥላ አላፊ ነው *እምነ ረሃብ የኄይስ ኩይናት ከረሀብ ጦርነት ይሻላል። *ለዘየአምን ኩሉ ይትከሃል ለሚያምን ሁሉ ይቻላል *ሕማማ ለዐይን ርዕየተ ጸላኢ ያይን በሽታዋ ጠላትን ማየቷ *እለ ከርሦሙ አምላኮሙ ሆድ አምላኪዎች *ሀብ ለኩሉ ለዘሰአለከ ለለመነህ ሁሉ ስጥ *በቁስለ ዚአሁ ሀዮነ ቁስለነ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን *አኮ ለዘሮጸ ባህቱ ለዘበደረ ለሮጠ አይደለም ለቀደመ እንጅ *አፍቅር ቢጸከ ከመ ነፍስከ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ *እስመ ፍቅር ከመ ሞት ጽንእት ፍቅር እንደሞት ጽኑ ናት። *ሕይወት ወሞት ውስተ እደ ልሳን ህይወትም ሞትም በአፍ ይመጣሉ *መኑ ከመ አምላከነ? እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን አለ? *አኮ በሲበት አላ በአእምሮ በሽበት አይደለም፤በማስተዋል እንጅ *ህብ ፍኖተከ ለእግዚአብሔር መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ *ሀቡ ዘነጋሢ ለነጋሢ፤ወዘተረፈእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር የቄሳርን ለቄሳር፤የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ። ...
Comments
Post a Comment